Tag Archives: Oyster mushroom

ስለ ዕንጉዳይ አጠቃላይ መረጃ

እንጉዳይ የተወሰኑ የፈንገስ ዝርያዎች የመራቢያ አካል ነው፡፡እንጉዳይ በተፈጥሮ በጫካ ውስጥ፣በሜዳ ላይ፣ ሕይወት ባለው ዛፍና እየበሰበሰ ባለ የዛፍ ግንድ ላይ ያድጋል፡፡ ባሁኑ ወቅት ግን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለእንጉዳይ እድገት አስፈላጊ የሆኑትን ንጥረ- ነገሮችንና የአየር ሁኔታዎችን በሟሟላት በቤት ውስጥ ማምረት ተችሏል፡: ዕንጉዳይ በፕሮቲን ይዘቱ ሶስተኛ ደረጃን ይይዛል፡፡ በእንቁላልና በስጋ ብቻ ሲበለጥ፡፡ ለህፃናት ጤናማ ህይወት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

ዕንጉዳይ   ጣፋጭ በሆነ የስጋ ጣዕም የታደለ ነው፡፡  ከማንኛውም የምግብ አይነት ጋር ተቀላቅሎ ሲሰራ ምግቦችን ጣፋጭና አርኪ ያደርጋቸዋል፡፡ዕንጉዳይ በንጥረ ነገር ይዞታው የተመሰከረለት ነው፡፡ ሁሉንም አበይት አሚኖ አሲዶችን፣ ቫይታሚኖችንና ሚኒራሎችን ይይዛል፡፡ ዕንጉዳይን ከስጋና ከዕንቁላል የሚለየው ለደም ግፊትና ለልብ ህመም ዋንኛ ጠንቅ የሆነውን ኮሌስትሮል ባለመያዙ ነው፡፡ ከስጋና ከዕንቁላል ምግቦች ወደ ዕንጉዳይ ማተኮር ብልህነት ነው፡፡

የተለያዩ የእንጉዳይ አይነቶች እጅግ የተመሰከረላቸው የፈውስ ሀይል አላቸው፡፡እነዚህም በባክቴሪያ  የሚከሰቱ በሽታዎችን

በቫይረስ የሚከሰቱ በሽታዎችን

በጥገኛ ህዋሳት የሚከሰቱ በሽታዎች

የደም ግፊት በሽታን

የካንሰር በሽታን

አርተርዮስክለሮሲሰ

የጉበት በሽታን የዳያቤቲክ በሽታን   በመፈወስ፣ በማሻልና በመከላከል ይታወቃሉ፡፡  እንዲሁም የሰውነትን የመከላከያ ስርዐትን በማጎልበት ለበሽታዎች እንዳንጋለጥ ያደርጋሉ   ከዚህም በላይ ዕንጉዳዮች ቀላል የማይባል የአንታይ ኦክሲዳንት ባህሪ ስላላቸው አጠቃላይ ሰውነትን ለማደስና ለማጎልበት ይረዳሉ፡፡ ሺታኬ፣ ሬይሺ እና ሚቴክ(ሄን ኦፍ ዘ ውድስ) እጅግ በረቀቀ የፈውስ ሀይላቸውና ሰውነትን የማደስ ብቃታቸው የታወቁና ተፈላጊ የዕንጉዳይ ዝርያዎች ናቸው ፡፡

የዕንስሳት ተዋፅዖ ውጤት ምግቦች በአሳሳቢ ሁኔታ እያደገ ያለውን የአለማችንን ሕብረተሰብ የፕሮቲን ፍላጎት ማርካት አለመቻላቸው የታወቀ ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን በማደግ ለይ ያለው የአለም የዕንጉዳይ ምርት ነው ይህንን ክፍተት ይሞላል ተብሎ የሚጠበቀው፡፡ ሰለሆነም ዕንጉዳይን የማምረት ስራ ተፈላጊና አትራፊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሁንም እየሆነ ነው፡፡ ማስረጃውም ሕብረተሰባችን ለዕንጉዳይ ያለው ትኩረት እያደገ መምጠቱ ነው፡፡

እነዚህን ግሩም የሆኑ የዕንጉዳይ ዝርያዎችን ለማምረት የሚያስፈልገው እንደ ሰብል ገለባ ያሉት ብዙ ዋጋ የማይሰጣቸው የግብርና ተረፈ ምርቶች ብቻ መሆናቸውም አስደናቂ ነው፡፡ዕንጉዳይ በተለያየ መልክ ተሰርቶ ለምግብነት ይቀርባል፡፡ ከነዚህም መሀከል ሾርባ፣ በርገር፣ ወጥና ከፒዛ ጋር ሊሰራ ይችላል፡፡ ባሁኑ ግዜ ዕንጉዳዮች በእንክብልና በሽሮፕ መልክ ተሰርተው ለተጠቃሚ ይቀርባሉ፡፡ አነዚህም ውጤቶች አንደ ቅመም ጣዕምን መጨመርና ጤናማነትን የሚያጎናጽፉ ውጤቶች በመባል ይታወቃሉ፡፡ በአሁኑ ግዜ ለራስ አርካታም ይሁን ለንግድ ስራ ዕንጉዳይን የማምረት  አለም አቀፍ  ስራ ሆኖአል፡፡ የዕንጉዳይ አመራረት ስልጠና የተሳተፈ ማንኛውም ሰው ዕንጉዳይን ማምረት ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሳ የገንዘብ አቅሙን መገንባትና በሚያመርተው የዕንጉዳይ መልካም ፕሮቲን የተመጣጠነ ምግብ በማግኘት ጤናውን መጠበቅ  ይችላል፡፡  ስራ ለሌላቸውም እንደ አዲስ የስራ መስክ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለአነስተኛ ደረጃ ዕንጉዳይ ምርት በአነስተኛ ቤት ውስጥ መመረት መቻሉና ሰፊ ባዶ መሬት አለማስፈለጉ የብዙ ሰዎችን ቀልብ መሳብ ችለዋል፡፡

በአለም ላይ ከሚመረቱት የዕንጉዳይ አይነቶች ኦይስተር ተብሎ የሚጠራው የሶስተኛን ደረጃ ሲይዝ በኢትዮጵያ ግን  የአንደኛ ደረጃን ይይዛል፡፡   

ሥዕል 4 ኦይስተር ተብሎ የሚጠራው የዕንጉዳይ ዝርያ

ኦይስተር የብዙ ዕንጉዳይ አምራቾች ምርጫ ከሆነበት ምክኒያቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ፡፡

  1. በቆላማ የአየር ጠበይ ባላቸው አካባቢዎች ማደግ መቻሉ፡፡
  2. ኦይስተር ማደግ የሚችልባቸው የግብርና ተረፈ ምርቶች ውስን አለመሆን፡፡
  3. ኦይስተርን ማሳደግ የሚችሉ የተለያዩ የግብርና ተረፈ ምርቶች በብዛት መገኘት፡፡
  4. ከተዘራበት እስከ ምርት የሚሰበሰብበት ያለው ግዜ አጭር መሆኑ፡፡ በአማካይ 30 ቀናት ያልበለጠ፡፡
  5. የሰብልና የቡና አምራቾች ዕንጉዳይን በማምረት የሰብልና የቡና ተረፈ ምርቶችን ለዕንጉዳይ ማምረቻ፤ ዕንጉዳይ ተመርቶ ሲያበቃ የሚቀረውን ስፔንት ተረፈ ምርት ደግሞ ለሰብል እርሻ መሬት ማዳበሪያነት በመጠቀም ሁለቱን ማጣመር መቻሉ፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሀብትን በብቃት መጠቀም ያስችላል፡፡
  6. ትንሽ ክብደት ያለውን የግብርና ተረፈ ምርት ወደ ብዙ ትኩስ የዕንጉዳይ ምርት የመቀየር ብቃቱ(biological efficiency) ፡፡ ይህም ብቃት በአማካይ ከ 97 – 150 % ይደርሳል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከ 5 ኪግ የጥጥ ፍሬ ገለባ አስከ 5 ኪግ የሚደርስ ትኩስ የዕንጉዳይ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡